November 9, 2026
2 min readከመጽሐፍ ገጾች | ክፍል ፪ Notes from Underground (በ Fyodor Dostoevsky)
By 👑 ነጋድራስ መሳፍንት🛡️

**📚 ከመጽሐፍ ገጾች | ክፍል ፪
የሳምንቱ መጽሐፍ፦ Notes from Underground (በ Fyodor Dostoevsky) **
የትኩረት ነጥብ፦ የሰው ልጅ የራሱን ጥቅም የሚቃወምበት እንቆቅልሽ እና የ"Self-Sabotage" (ራስን የማጥፋት) ስነ-ልቦና!
ቤተሰብ👋
በዚህ ሳምንት "ከመጽሐፍ ገጾች" ዓምዳችን፣ የሰውን ልጅ ውስጣዊና የተደበቀ ስነ-ልቦና በመመርመር ወደር የማይገኝለትን የሩሲያዊውን ታላቅ ደራሲ ፊዮዶር ዶስቶየቭስኪ Notes from Underground የተሰኘውን መጽሐፍ እንመለከታለን።
በትሬዲንግ ዓለም ውስጥ ሁላችንም የምንጠይቀው አንድ እንቆቅልሽ የሆነ ጥያቄ አለ፦ "ትክክለኛውን ስትራቴጂ እያወቅን፣ ስቶፕ ሎስ አለመጠቀም አካውንት እንደሚያጠፋ እያወቅን፣ ከዕቅድ ውጭ መግባት (Overtrading) እንደሚጎዳን በሚገባ እየተረዳን... ለምንድነው መልሰን ያንኑ ስህተት የምንደግመው?"
ከ150 ዓመታት በፊት ዶስቶየቭስኪ ይህንን የሰው ልጅ እንቆቅልሽ በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ፍርጥርጥ አድርጎ ገልጾታል። በዚያ ዘመን የነበሩ ፈላስፎች "የሰው ልጅ ምክንያታዊ ፍጡር ነው፤ ስለዚህ የራሱን ጥቅምና ህግ ካሳየኸው ሁሌም ትክክለኛውን ነገር ያደርጋል" ብለው ያምኑ ነበር። ዶስቶየቭስኪ ግን ይህንን አጥብቆ ተቃወመ። እንዲህም አለ፦ "የሰው ልጅ ምንም ያህል ምክንያታዊ ህግ ብታስቀምጥለት፣ አንዳንድ ጊዜ ነፃ ፈቃዱን (Free Will) ለማረጋገጥ ብቻ ሲል፣ የሚጎዳውን ነገር እያወቀ ሆን ብሎ የራሱን ጥቅም የሚቃወምና ህግ የሚጥስ ፍጡር ነው!"
ይህ የዶስቶየቭስኪ ጥልቅ የስነ-ልቦና ግኝት በቻርት ፊት ስንቀመጥ የሚገጥመንን "ራስን የማጥፋት አባዜ" (Self-Sabotage) ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፦
1.ዕውቀት ብቻውን ከስህተት አያድንም፦ ዶስቶየቭስኪ እንደሚለው፣ የሰው ልጅ ሁለት ሲደመር ሁለት አራት መሆኑን ያውቃል፤ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ስሜቱ ሲነሳበት "ሁለት ሲደመር ሁለት አምስት ቢሆን ደስ ይለኛል" ብሎ ከእውነታው ጋር ይላተማል። በትሬዲንግም፣ ገበያው እየወደቀ መሆኑን (Downtrend) ዓይንህ እያየ፣ ውስጣዊ እልህህ ግን "አይ አሁን መመለስ አለበት" ብሎ እንድትገዛ (Buy እንድታደርግ) ያስገድድሃል። ችግሩ የዕውቀት ማነስ ሳይሆን፣ ለእውነታው እጅ ያለመስጠት የውስጥ አመጽ ነው::
2.በህግ የመሰላቸት አደጋ፦ የመጽሐፉ ገጸ-ባህሪ ሁሉም ነገር በቀመርና በህግ ሲታጠር ይጨንቀዋል፤ ስለዚህ ሰላሙን ለማደፍረስ ሆን ብሎ ትርምስ ይፈጥራል። አንድ ትሬደር ለሳምንታት ህጉን አክብሮ በትንሽ በትንሹ ትርፍ ከሰራ በኋላ፣ በድንገት አንድ ቀን ምንም ምክንያት ሳይኖረው ትልቅ ሎት ከፍቶ የሳምንታት ልፋቱን በአንድ ሰዓት ውስጥ ያጠፋል። ለምን? ምክንያቱም ያልተገራው የውስጥ ማንነቱ በዲሲፕሊኑ ስለተሰላቸ፣ ነፃነቱን ለማወጅ ሲል የራሱን ህግ ይሰብራል!
3.በቀል ትሬዲንግ (Revenge Trading) እንደ ህልውና ትግል፦ ገበያው ስቶፕ ሎስ ሲመታን፣ አእምሯችን ያንን የሚቀበለው እንደ ገንዘብ መቀነስ ብቻ ሳይሆን እንደ ክብር መነካት (Ego Injury) ነው። እናም ልክ እንደ ዶስቶየቭስኪ ገጸ-ባህሪ፣ ገበያውን ለማሸነፍና "እኔ ልክ ነኝ" ለማለት ስንል፣ ማሸነፍ እንደማንችል እያወቅን ወደ እሳቱ እንገባለን።
4.ውስጣዊውን "የመሬት ውስጥ ሰው" (The Underground Man) መግራት፦ በሁላችንም ውስጥ ምክንያታዊው እቅድ አውጪውና ሰከን ያለው ማንነት እንዳለ ሁሉ፤ በስሜት የሚነዳ፣ ህግ መጣስ የሚፈልግና እልኸኛ የሆነ ሌላ ማንነት አለ። ይህንን ውስጣዊ ጠላት ማሸነፍ የሚቻለው "እኔ ምንም ስሜት የለኝም" ብሎ በመካድ ሳይሆን፣ መኖሩን አምኖ በጠንካራ የስጋት ቁጥጥር (Risk Management) እጁን በማሰር ነው።
ቤተሰብ፣ ትልቁ የትሬዲንግ ጦርነት የሚካሄደው በለንደን ወይም በኒውዮርክ የገበያ ክፍለ-ጊዜያት ውስጥ አይደለም የሚካሄደው በእኛው አእምሮ ውስጥ በምክንያታዊነታችን እና በስሜታዊነታችን መካከል ነው። በውስጣችን ያለውን ህግ ጣሽ ስሜት ነቅተን እንጠብቀው፤ ለራሳችን ጥቅም ጠላት ከመሆን ወጥተን የራሳችን ምርጥ ወዳጅ እንሁን!
መልካም የንባብና የትሬዲንግ ሳምንት!
✍️ ነጋድራስ መሳፍንት
የነጋድራስ አእምሮ | ለአሸናፊ ትሬደሮች የሚሆን የአመለካከት ከፍታ!**
30-02-2019 ዓ.ም**
Discussion (9)
thx
thx
Tnks bro
ገራሚ የሆነ ትምህርት
wow
wow
Tanks
Tanks
Tanks